Get Mystery Box with random crypto!

ሕወሃት በአፋር ክልል የተፈፀመው ወረራ ባደረሰው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ሳቢያ በክልሉ ከ1.3 | YeneTube

ሕወሃት በአፋር ክልል የተፈፀመው ወረራ ባደረሰው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ሳቢያ በክልሉ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብ ለጉዳት ተጋልጧል ተባለ፡፡

ቡድኑ በአፋር ክልል 21 ወረዳዎች ላይ ባደረሰው ጥቃት ከ360,000 በላይ ዜጎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውም ተነግሯል፡፡

ጉዳት በደረሰባቸው በእዚሁ ወረዳዎች የሚገኙ እንደ ትምህርት ቤትና ሆስፒታል ያሉ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሙሉ በሙሉ መውደማቸው የተነገረ ሲሆን ዜጎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ ናቸው ተብሏል፡፡

ይህን የሰማነው በአፋር ክልል በጦርነቱ ምክንያት ለደረሰው ጉዳት ድጋፍ ለማሰባሰብ በአዲስ አበባ የተቋቋመው ግብረ ሀይል መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው፡፡

የአፋር ልማት ማህበር ከአፋር ተወላጆችና ወዳጆች ጋር በመሆን ያቋቋመው ግብረ ሀይል በህወሃት ወረራ ምክንያት ለተፈናቀሉት ዜጎች፤ ቡድኑን ለመፋለም ለዘመቱትና ለቤተሰቦቻቸው ድጋፍ ለማሰባሰብ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግሯል፡፡

የግብረ ሀይሉ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዘሀራ ዑመድ የአፋር ህዝብ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት እየከፈለ ላለው መስዋዕትነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ አጋርነቱን ሊያሳይ ይገባል ብለዋል፡፡

የአፋር ህዝብ ከጦርነቱም ቀድሞ በጎርፍ ፣ በአንበጣ እና በድርቅ ምክንያት ብዙ ፈተና ያየ ህዝብ መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ ዘሀራ አሁን የደረሰበት ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖበታል ብለዋል፡፡

ህወሃት ጥቃት ከፈፀመባቸው አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ተቀብለው ያስተናገዱ የነበሩ የክልሉ ነዋሪዎች በተደራረበባቸው ችግር ምክንያት ራሳቸውም እርዳታ ፈላጊ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

የህወሃት ቡድን በአገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ የፈፀመው ዝርፊያና ውደመት በቃላት ለመግለፅ የሚከብድ መሆኑን ያብራሩት ወ/ሮ ዘሀራ ቡድኑ የህክምና ቁሳቁስ መዝረፍ አልበቃ ብሎት ይዞ መሄድ ያልቻላቸውን አውድሞ ወጥቷል ብለዋል፡፡

የአፋር ህዝብ ሀብት የሆኑ የቁም እንስሳትን ጭምር በጥይት ደብድቦ መግደሉን ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባ በሚኖሩ የአፋር ተወላጆች የተቋቋመው የድጋፍ አሰባሳቢ ግብረ ሀይል በክልል ደረጃ ከተቋቋመው አቢይ ኮሚቴ ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ሰምተናል፡፡

የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ ከፈቀዳችሁ በአዲስ አበባ አዋሬ አካባቢ በሚገኘው የሱልጣን አሊ ሚራህ መስጊድ እየመጣችሁ አድረሱን ብለዋል፡፡

የትኛውንም ዓይነት ድጋፍ ከምስጋና ጋር እቀበላለሁ ያለው ግብረ ሀይሉ የገንዘብ ድጋፍ የምታደርጉ ደግሞ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000444559512 ሒሳብ ቁጥር በኩል ማስገባት ትችላላችሁ ብሏል፡፡

[Sheger]
@YeneTube @FikerAssefa